ለምርትና አገልግሎት ጥራት ተወዳዳሪዎች 4ኛው ዙር ሀገራዊ የእውቅና ሽልማት ተሰጠ

ለምርትና አገልግሎት ጥራት ተወዳዳሪዎች 4ኛው ዙር ሀገራዊ የእውቅና ሽልማት ተሰጠ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለ4ኛው ዙር የኢትዮጵያ የምርት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ተወዳዳሪዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ ሥነ-ስርዓት ላይ ሀገራዊ የእውቅና ሽልማት ሰጥተዋል፡፡

ክቡር ፕሬዝደንት ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ተፈፃሚ ለማድረግ ምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚገባ ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ጀምሮ ይበልጥ ትኩረት እንደተሰጠው ገልፀዋል፡፡

የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋነኛው ዓላማ የግብርና ልማትን ማዘመን፤ የኢንዱስትሪ፣ የወጪ ንግድና የአገልግሎት ዘርፉን ማስፋት እንደሆነ ጠቅሰው በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ለተያዘው ውጥን የምርት እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትና ተወዳዳሪነት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን መንግስት ብቻ የሚያደርገው ጥረት በቂ ባመሆኑ ሁሉም የልማት አጋሮች የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ተወዳዳሪነትን መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የግሉ ዘርፍ የኢንተርፕሪነርሽፕና የልማታዊ አስተሳሰቡን በማሻሻል ምርታማነትን፣ ጥራትንና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰው ሀገራዊ ባለሀብቶች ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን መምራት የሚያስችል ዘመናዊ የዕውቀት፣ የክህሎትና የልምድ ማነስ ክፍተቶችን ለመሙላት በሥራ አመራር፣ በግብይት፣ በምርት ጥራትና ቁጥጥር፣ በምርምርና ስርፀት፣ በመረጃ ሥርዓትና በቴክኖሎጂ ሙያ ብቃት ራሳቸውን ማጠናከርና ማዘመን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በየመስኩ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ብሎም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ሀገራዊ ራዕይን እውን ለማድረግ ጥራትን መሰረት አድርጎ መስራት የማይታለፍ ተግባር በመሆኑ በአገልግሎት፣ በአምራችና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ የልማት ተዋናዮች ሁሉ ጥራትንና ተወዳዳሪነትን መሰረት አድርጎ መስራት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ክቡር ፕሬዝደንት አሳስበዋል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ የምርት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶች በጥራትና በተወዳዳሪነት መሰረት ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ እስካሁን ሶስት ተከታታይ የሽልማት ስነስርዓቶችን አካሂዶ ተቋማት የአመራረትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታቸውን ፈትሸው ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው ለሽልማት እንዲበቁ በማድረግ የተሸለሙት የበለጠ እንዲበረታቱ ያልተሸለሙት ደግሞ ክፍተቶቻቸውን አርመው ለወደፊት ተሸላሚ የሚሆኑበትን አሰራር እንዲዘረጉ ያስቻለ ሲሆን አሁን ለአራተኛ ዙር ሽልማት ማዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ክቡር ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቋማት ጥራትን መሰረት አድርገው እንዲሰሩና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ገበያ ላይ ብቁና ተወዳሪ እንዲሆኑ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው በቀጣይነት እየተከናወነ ያለው የጥራት ሽልማት ሥነ-ስርዓት ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ገፅታ ግንባታ ካለው ፋይዳ አንፃር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው በመሆኑ ለውድድሩ ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

በ4ኛው ዙር የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ከክቡር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አንዱ ናቸው፡፡

ዶ/ር አድማሱ እንዳሉት ድርጅቶች አሰራራቸውን ፈትሸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራት ወሳኝ መሆኑ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን በመቅሰምና ሀገራዊ የጥራት መስፈርቶችን ቀርፆ በመንቀሳቀስ ስኬት እያስመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ2000 ዓ.ም ተመስርቶ በ2001፣ በ2003ና በ2006 ዓ.ም 150 ድርጅቶችን አወዳድሮ 24 ተቋማትን የሸለመ ሲሆን አሁን አራተኛውን ዙር እንዳከናወነ ታውቋል፡፡ ለዚህ ሽልማት 55 ድርጅቶችን አወዳድሮ አምስት ተቋማትን በ1ኛ ደረጃ፣ አንድ ድርጅት በ2ኛ ደረጃና አምስት ድርጅቶችን ደግሞ በ3ኛ ደረጃ በድምሩ 11 ተቋማትን ሸልሟል፡፡

የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ኢትዮጵያ ቆዳ አክስዮን ማህበርና ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ እንደ ቅደም ተከተላቸው የአንድኛ ደረጃ ከፍተኛውን የክብር ዋንጫ ሽልማት ያሸነፉ ተቋማት እንደሆኑ ከነበረው የሽልማት ሥነ-ስርዓት መገንዘብ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ድርጅቶችን በአራት መስኮች ተመስርቶ የሚመርጥ ሲሆን አምራች፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ አገልግሎት ሰጪ፣ ለትርፍ የተቋቋሙ አገልግሎት ሰጮ እና ኮንስትራክሽን /ግንባታ/ በሚሉ መስኮች የሚለዩ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ድርጅቱ በስምንት ዓመታት ጉዞው ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ሲሆን ከህብረተሰብ የግንዛቤ እጥረት የተነሳ ከጥራት ይልቅ ለዋጋ ቅድሚያ መስጠትና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጅቶችን ያለውድድር በገንዘብ ክፍያ ብቻ የጥራት ሽልማት የሚሰጡበት አግባብ እየጨመረ መምጣት ተጠቃሽ እንደሆኑ 4ኛውን ዙር ሽልማት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የድርጅቱ መጽሔት አብራርቷል፡፡

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት

Related posts

Leave a Comment