የመምህራን የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር በድምቀት ተካሄደ

የመምህራን የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር በድምቀት ተካሄደ
 
ሰኔ 11/2008 ዓ/ም « ክብርና ምስጋና ለህዳሴው ትውልድ አናጺ መምህራን » በሚል መሪ መልዕክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና መምህራን ማህበር በጋራ የተሻለ አፈጻጸም ላላቸው 128 መምህራን ፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄዱ፡፡
 
በመርሃ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው፤ « መምህራን የመማር ማስተማር ሥራ እንዲሻሻል የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በከፈሉት መስዋዕትነት በልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ለውጥ መታየት ጀምራል ከማለታቸዉም ባሻገር የሚታየውን የትምህርት የጥራት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመምህራን ድርሻ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
ክቡር ሚኒስትሩ መንግሥት የመምህራንን ትውልድ የማነጽ ከፍተኛ ኃላፊነት ተረድቶ ልዩ ማበረታቻዎችን ለመምህራን ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው፤ «በቅርቡ በከተማዋ የሚገኙ መምህራን ከግንቦት 1/2008 ዓ/ም ጀምሮ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል » በማለት ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ከሁለት እርከን ይጀምር የነበረው የመምህራን ደመወዝ ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ስምንት እርከን ተጨምሮ በ10 እርከን እንዲጀምር ፣ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ለሚገኙ መምህራን አምስት ሺ የመኖሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውንና ሌሎች 19 ሺ የመኖሪያ ቤቶችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
 
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንደተናገሩት ፤ መምህርነት የሁሉም ሙያዎች መነሻ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በእውቀትና ስነ ምግባር አንጸው ለውጤት የሚያበቁ መምህራን መሆናቸውን በመገንዘብ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል ፡፡ በመምህርነት ሙያ ህዝብን የሚያገለግሉ የላቀ ሙያ ባለቤት በመሆናቸው መንግሥት ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል በማለት የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል የተዘረጋው መርሃ ግብረ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
 
ዘገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ነው

Related posts

Leave a Comment